ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ 2ሺህ 885 ተማሪዎችን አስመረቀ

Share this story

Posted on: Jul 19,2018

መንግስት ለከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን በየአካባቢው ከፍቶ የአካባቢው ማህበረሰብ ከተቋሙ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም መንግስት በ1999 ዓ.ም ከከፈታቸው 13 የከፍተኛ የትምህርት ተቋሟት ውስጥ አንዱ ነው፤ ከተመሰረተም 12ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ስራ ሲጀምር 754 ተማሪዎችን በመቀበል ነበር፡፡

አሁን ላይ የቅበላ አቅማችንን ከ4000 በላይ አድርሰነዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች ተቀብሎ ስራ ሲጀመር 13 የነበሩትን መደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች በየጊዜው በማሳደግ 40 አድርሶታል፡፡ በሌላ በኩል ለሁለተኛ ዲግሪ ስርዓተ-ትምህርት የፀደቀላቸው 32 ፕሮገራሞች ሲኖሩን ከእነዚህ ውስጥ 18ቱ በመደበኛ፣ በክረምት፣ በማታ እና በቅዳሜና እሁድ ፕሮገራሞች ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩና እያስመረቁ ይገኛሉ፡፡

የእዚህ ዓመት የተማሪዎቻችን ቁጥር በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም 11000፣ በተከታታይና ርቀት ትምህርት 1400 እንዲሁም በክረምት ፕሮግራም 6247 ተማሪዎችን በመቀበል ጠቅላላ የተማሪዎቻችንን ቁጥር 18,647 ደርሷል፡፡ በእዚህም በአለፉት ዓመታት ዩኒቨርሲቲያችን ብቃት ያለቸውን ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ ወይም የትምህርት ዘርፎች እያስመረቀ ለሀገራችን ልማትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 885 ተማሪዎችን ሰኔ 23/2010 አስመረቀ።የከፍተኛ ማዕረግ ምሩቃን በበኩላቸው በቀሰሙት እውቀት በመታገዝ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የለውጥ ጅማሮ ከዳር ለማድረስ እንደሚተጉ ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለ10ኛ ጊዜ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት በመደበኛና በክረምት መርሃ ግብሮች የተከታተሉ ናቸው።በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከተመረቁት አጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 2ሺህ 830 በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን 55ቱ የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቃን ናቸው፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 1ሺህ 30ዎቹ ሴቶች መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የተዘጋጀውን የወርቅ ሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማቶች የሰጡት የኢፌድሪ የግብርናና የእንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰባሳቢ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ ናቸው፡፡

ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት “ዩኒቨርሲቲዎች ብቃት ያለው ባለሙያ በማፍራትና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ይበልጥ በማስፋት ድህነትን ከአገሪቱ ለመቀነስ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይገባዋል” ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ህብረተሰብ የትምህርት ዕድል በማመቻቸት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ትምህርት መርሃ ግብርን በማስፋፋት ድሬዳዋ የምስራቁ የኢንዱስትሪ ኮሪደር የማድረጉ ራዕይ እንዲሳካ ዩኒቨርሲቲው ተግቶ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡

አያይዘውም “የዛሬ ተመራቂዎች ሥራ ጠባቂ ሳትሆኑ ሥራ ፈጣሪ በመሆን አገሪቷ በምታራምደው የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ጉዞ ውስጥ በመደመር በተማራችሁት ሙያ አሻራችሁን ማስቀመጥ ይጠበቅባችኋል” በማለት የዘንድሮን ምረቃ ልዩ የሚያደርገው ሀገራችን የነዳጅ በለቤት በሆነችበት ማግስት መሆኑ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ሥራን ለመፍጠር ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ መስሪያ ቤቶችና ኢንዱስትሪዎች

ጋር የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከቻይና የመጡ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተወካዮች የዘንድሮ የቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ተመራቂ ተማሪዎችን ለስድስት ወር ወደ ቻይና ወስደው ስልጠና በመስጠት ለመቅጠር እንዳቀዱ ለዩኒቨርሲቲው መግለጻቸውንም አመልክተዋል።

ዶ/ር ያረድ ማሞ በመጨረሻም ያስተላለፉት መልዕክት በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቁ ቤተሰቦቻችሁን የምታስመኩ፣ ዩኒቨርሲቲያችሁን የሚታስከብሩና ሀገራችሁን የምታኮሩ ዘጎች ትሆኑ ዘንድ የልብ መሻቴ ነው፡፡

ይህ ደግሞ ይቻላል፡፡ ዕድሜ ልክ አንብቡ፣ዕውቀትና በብርቱ እሹ፣ እራሳችሁን አክብሩ፣ ራሳችሁን ሁኑ፣ ያላችሁን አካፍሉ፣ ግደታችሁን ተወጡ፣ መጪያችሁን አልሙ፣ በብላሃት ወስኑ፣ ለህይወት ውጣ ውረድ በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ፣ የትም ብትሆኑ የትወላጆቻችሁን፣ መምህራኖቻችሁን፣ ዩኒቨርሲቲያችሁን፣ ሀገራችሁን አትዘንጉ በማለት ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከዘንድሮ ተመራቂዎች መካከል 3.96 በማምጣት የወርቅ መዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኮከብ ተመራቂ መድኃኒት ፉአድ ባገኘችው ዕውቀት አገሯን ለማገልገል እንደምተሰራ ገለፀች።

በአገሪቱና በህዝቦች መካከል የፍቅር፣ የአንድነትና የዕድገት ዘመን ለማምጣት እየሰሩ የሚገኙትን የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የዶ/ር አብይ አህመድ ዓላማ ለማሳካት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ የ2010 የወርቅ ተሸላዎች ከቤተ-መንግስቱ ጀምሮ የተለያዩ ቦታዎችን እንዲሚጎብኙ ቃለ መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡ የእዚህ አመት የወርቅ ተሸላሚዋ ይህ እንደሚያገጓገጓት ገልፃለች፡፡ ከዶ/ር አብይ ጎን እንደምትሆንና የጀመሩትን ዓላማ ዳር ለማድረስ ኃላፊነቴን እንደምወጣ አረጋግጥላቸዋለሁ ብላለች፡፡

“የተማርን ወጣቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዓላማ እንዲሳካ እውቀታችንና ጉልበታችንን አንሰስትም፤ ከሳቸው ጋር በመደመር ድህነትን ከአገሪቱ ለማጥፋት ቀንና ማታ እንሰራለን” ያለው ደግሞ 3.9 በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ከተማ ዳዲ ነው፡፡

በኢንጂነሪንግ ትምህርት 3.88 በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው አቡሽ ፍቃዱ በበኩሉ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን እየተጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር የዶ/ር አብይ ዓላማ እንዲሳካ የድርሻውን እንደሚወጣ አመልክቷል።