የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ የጥናት ውጤት ግብአት ማሰባሰቢያ ላይ ውይይት አካሄደ

Share this story

Posted on: Oct 09,2018

ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ለውይይት በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ከመስከረም 28-30/2011 የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በተለያዩ መድረኮች እየተወያየ ይገኛል፡፡

በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው መሠረት ባለፉት ሃያ አራት አመታት በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሁሉም ዘርፎች የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን በማስፋፋት የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት በማጐልበት በኩል በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ውጤቶችም ተመዝግበዋል፡፡ በተለያዩ መስኮች ባለሙያዎችን በማፍራት አገራችን አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን ከመነሻችን ሲታይ የተመዘገቡት ውጤቶች ከፍተኛ ቢሆኑም አሁንም ለሁሉም ሕጻናትና ወጣቶች ትምህርትና ሥልጠናን ማድረስ አልቻልንም፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ጥራትና አግባብነትን በተመለከተ በሁሉም የትምህርትና ሥልጠና ዘርፎች በተለይ የተማሪዎችን የመማር ውጤት ከማሻሻል አኳያ በፖሊሲው የተቀመጠውን የመማር ውጤት በማረጋገጥ በኩል ችግሮቹ የገዘፉ ናቸው፡፡ ይህም አገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት ካደረግንባቸው የዘላቂ ልማት ግቦች አኳያ ምናሳየው አፈጻጸማችን ችግሮች ይስተዋሉበታል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ይቻል ዘንድ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ለዚሁ ጥናት ግብአት የሚሆኑ ሃሳቦችን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንደ ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡